የአገራችን ጊዜያዊ ሁኔታና የአማራው የሕልውና ትግል
በቅርብ ጊዜ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ ከመጨረሻው ጥግ ደርሷል። ኢትዮጵያን አገር ከማድረግ አንስቶ እስከ ዘመናዊ ሥልጣኔን ማስፋፋት ድረስ የአማራው ሚና ምን እንደነበር ሁላችን እናውቃለን። ከዚህ አኳያ አማራው ሊኖረው የሚገባው የፌዴራል መንግሥት ቦታና አሁን ይዞ ያለው ቦታ፤ ሰማይና ምድር ናቸው። ይሄ ቀጣይ የሆነው የቅርብም ሆኑ የሩቅ ጠላቶቻችን፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት አማራውን ማጥቃት በሚል መርኅ፤ ያካሄዷቸውና ሳይሳካላቸው የቀሩት ተደጋጋሚ ወረራዎች ቀጣይ ሂደት ነው። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት፤ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለው በደል፤ የተቀነባበረ ዘር የማጥፋትና ከያካባቢዎች አማራውን የማጽዳት ወንጀል ነው። ባሁኑ ሰዓት፤ አክራሪ የኦሮሞ ፅንፈኞች የፌዴራል መንግሥቱን በጃቸው አስገብተው፤ በአማራው ላይ እያደረጉ ያሉትን ጥቂቶቹን እንመለከት፤
አዲስ አበባ የአገሪቱ ማዕከልና የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ ሆና ሳለ፤ የከተማዋን የሕዝብ ስርጭት ለመለወጥና የኦሮሞ ከተማ ለማድረግ የሚደረገው ሩጫ፤ ብዙ የከተማዋ ነዋሪዎችን አፈናቅሎና የራሳቸውን የቤቶቻቸው ባለቤትነት እንዲያጡ እያደረገ ነው። በተለይም አማራን ከአዲስ አበባ ጨርሶ ለማጥፋት እየተደረገ ያለ ጥረት ነው።
በአማራው ወገናችን ላይ እየደረሰ ያለው የሕዝቡን ቁጥር መቀነስ ሁለተኛው ጉዳይ ነው። አማራውን በያለበት መግደልና ንብረቱን ማባከን፤ ማሰርና ማሳደድ፣ የአክራሪ ኦሮሞዎች የዕለት ተግባር ሆኗል። በአሁኑ ሰዓት ወጣት የአማራ ሴቶችን፤ ቤት ትዳር መሥርተው፣ ልጆች ወልደው ባገራቸው እንዳይኖሩ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማጓጓዙ፤ ሆን ተብሎ የታቀደ አማራውን ተተኪ የማሳጣት አካል ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተባብሮ ከሥልጣን ያስወገደው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ አሁን ተመልሶ በማንሰራፋት ላይ ነው። ይህ የፖለቲካ ሂደት፤ የአማራውን ሕልውና አደጋ የበለጠ አክሮታል። ባንድ በኩል የክልሉን የመሬት ይዞታ ጥያቄ፤ ማለትም የወልቃይት፣ የራያ፣ የጠለምት፣ የሁመራና የጠገዴ ሲያፈጥበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝብን በመጨረስና በማስጨረስ በወንጀል ተጠያቂ የሆኑትን የትሕነግ መሪዎች መልሶ የማቋቋሙ ሂደት፤ አገሪቱን አደጋ ላይ ጥሏታል።
የአሜሪካው የአገርና የውጪ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ብሊንከን፤ የእንቁልልጭ ብር ይዘው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማባበል ወደ አዲስ አበባ ተጉዘዋል። ሁሉን ነገር በጉልበቴ ካልሆነም በገንዘብ ደልዬ የኔ አሽከር አደርጋለሁ፤ የሚለው የአሜሪካ የውጪ ፖለቲካ፤ የምልህን አድርግ! የሚል መልዕክት ይዘው ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያነጋግሩ። ብሊንከን ለተቀጠፈው ሕይወት፣ ለወደመው ንብረት፣ ለተጨናጎለው የሰላምና የዕድገት ጅምር፤ ቅንጣት ታክል አዘነቴ የላቸውም። አንድና አንድ ተልዕኳቸው፤ የአሜሪካን የበላይነትና ጥቅም ማስጠበቅ ነው። መዘንጋት የሌለበት፤ የውጪ አገር፤ በተለይም በአሜሪካ የሚመራው የምዕራባዊያን ጥረት፤ በታሪክ ጠላታቸው አድርገው ያስቀመጡት አማራ፤ ጉልበቱንና አቅሙን፣ ታሪኩንና እምነቱን፣ ክብሩንና በራስ መተማመኑን ማውደም ነው። እናም የኒህ ግለሰብ ጉዞ ከዚህ አንጻር መታየት አለበት።
ይህ ሁሉ የሚደረገው፤ የአማራን፣ የኑሮ ሁኔታና የፖለቲካ ተሳትፎ ለመለወጥ ነው። እናም አማራው ይሄን ተረድቶ፣ ዛሬ በመሰባሰብ ላይ ነው። መንግሥታዊ ክንውኑን በማስተጓጎል፤ በአማራ ላይ የፌዴራል መንግሥቱ የያዘውን ዘመቻ፤ ወደ ማስቆሙ ተሰማርቷል። በአማራ መሀበራዊ ማሰራጫ ተቋሞች የአማራ ታዳሚዎች ቁጥር በጣም እየበዛ መጥቷል። በኢትዮጵያ ተዋሒዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ዙሪያ በተነሳው የመንግሥት ጣልቃ መግባት፤ ሁሉም በያለበት "ነግ በኔ!" ብሎ የዚህን ፅንፈኛ የኦሮሞ ገዢ ቡድን እንዲነሳበት አድርጓል። አሁን በያለንበት የትግል ተሳትፏችንን ከፍ በማድረግ፤ የአማራ ትብብርና አብሮ መነሳት ጥንካሬን ማሳየት አለብን። አማራ ታሪክ የሠራ፣ አማራ አገር ያነፀ፣ አማራ ከብዙዎች ጋር አብሮ መኖር የሚችልና የሚያውቅበት ነው። አማራው ራሱን ከጥፋት የመከላከል ታሪካዊ ግዴታ አለበት። አማራው አገሪቱን ካለችበት አዘቅት እንድትወጣ፤ መጀመሪያ የራሱን ሕልውና መጠበቅ አለበት።