የ ፻ ፳ ፯ ኛውን የአድዋ በዐል በተመለከተ በኢትዮጵያውያን ላይ በመንግስት ሃይሎች ስለተፈፀመው አሳፋሪ የግፍ ድርጊትን በተመለከተ ከአምባ የተሰጠ መግለጫ ፡፡
ታሪካችን የማንነታችን አካል ነው!
የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ ም
የዛሬ ፻፳፯ ዓመት በአድዋ የፈሰሰው የአርበኞቻችን ደም፤ ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት ገርፎ ለማባረር የተከፈለ መስዋዕት ነው። የዛሬው ምን ይባላል!
በ፻ ፳ ፯ ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ላይ የተፈጸመው ግድያና በዓሉ እንዳይከበር ክልከላ፤ በታሪክ ብሎም በማንነት ላይ የተደረገ ጥቃት ነው።
- የአድዋ ድል፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ልዕልናዋንና ልዑላዊነቷን ያስጠበቀችበት አኩሪ ታሪኳና የማንነታችን አካል ሆኖ ሳለ፤
- የአድዋ ድል፤ እኛ ከሁሉ በላይ ነን ያሉ አውሮፓውያንን ያሳፈረ የመላ ኢትዮጵያዊያን ድልና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ መላ ጥቁር ሕዝብ የኮሩበት ሆኖ ሳለ፤
- የአድዋን ድል ካለ አፄ ሚኒሊክ ዕውቀትና ብቃት፣ ካለ እቴጌ ጣይቱ ጥበባዊ ስልት፣ ከመላ ኢትዮጵያ በአንድነት ተሰባስበው አገራቸውን ከወራሪ ሊከላከሉ ከወጡት አርበኞች ቆራጥ ተጋድሎ ለይቶ የማይታሰብ ሆኖ ሳለ፤
- የአድዋ ድል ከትናቶቹና ከዛሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን፤ ከኢትዮጵያዊነት ተገንጥሎ የማይታይና የኢትዮጵያ ባለቤት እንድንሆን ያደረገን ሆኖ ሳለ፤
በዚች በአድዋ በዓል ቀን፤ ኢትዮጵያዊያን ተሰባስበው ቀደምት አርበኞቻቸውን ለመዘከር፣ ተጋድሏቸውን ለማውሳት፤ በማንነታቸው ለመኩራት ከያሉበት ሲወጡ፤ እኒህን አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፤ የአድዋን የድል በዓል ለማክበር እንዳይገኙ መከልከል፤ በቤተክርስትያናቸው ውስጥ በተሰበሰቡት ደግሞ ግድያና ድብደባ መፈጸም፤ የአገር አፍራሽነት ተግባር ነው፤ ፀረ የኢትዮጵያዊያን ነፃነትና ፀረ ኢትዮጵያዊነትም ነው። የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት በአንድ አገር ውስጥ መኖሩ አያስገርምም። ለዚህ ነው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየሀገሩ የሚገኙት። የአገር ታሪክ ግን፤ ለዚያውም አኩሪና ሌሎች በንክኪ የራሳቸው አድርገው የሚኮሩበት ታሪክ፤ የአገር ንብረት ሆኖ በያንዳንዱ ጎጥ በየዕለቱ የሚከበር መሆን ነበረበት። በዛሬው የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ግን፤ ይህ የሚወደድ ባለመሆኑ፤ ታሪክን ለመፋቅ፣ በማንነት እንዳንኮራ ለማድረግ፣ የአገር ዕሴትን ለማሳጣት የተደረገ ስለሆነ፤ አምባ ይሄንን አክርሮ ያወግዛል።
በዕለቱ የተከበሩ አባታችን እንደተናገሩት፤ የአድዋን ድልና ታሪክ የሚጠላ፤ ወራሪው ጣሊያንና የሱን ፈለግ የሚከተሉ ፀረ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። የመዋቾች ቤተሰቦችና የተደበደቡት አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ፍትኅን ከሕዝብና ከሕግ ይጠይቃሉ። በንፁሃን ላይ የተፈጸመው ወንጀል በመንግሥት ዕቅድ በመሆኑ፤ ለዚህ አሳፋሪ ተግባር ተጠያቂው የፌዴራሉ የብልፅግና መንግሥት መሆኑን እናስታውቃለን። ሕግን ሌሎች እንዲያከብሩ እያደረጉ፤ በኃላፊነት ስለተቀመጡ ከሕግ ውጪ ተግባር ፈጽመው ከፍርድ ነፃ መሆን አይቻልም።
የአማራ ምሁራንና ባለሙያዎች ስብስብ (አምባ)፤ በአዛውንት፣ በምዕመናን እና በሴቶችና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተደረገውን የመንግሥት ሕገ ወጥና ማን አለብኝ የግፍ ድርጊት በጥብቅ ያወግዛል።
አምባ በቅዱስ ጊወርጊስ ቤተክርስትያ ውስጥ የጭስ ፈንጅ በማፈንዳት በሕዝቡ ላይ የተፈጸመውን የግድያና የድብደባ ወንጀል በጥብቅ ያወግዛል።
ዛሬ አኩሪ የሆነው የአረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓለማ በመላው ዓለም በሚውለበለብበት ዘመን፤ ይሄንን ቀለም ያለበት ልብስ በአገራችሁ አትልበሱ በማለት ሕዝብን የሚያንገላቱ የመንግሥት አካላትን አምባ፤ ፋሺስቶችን የምናወግዛቸውን ያህል በጥብቅ ያወግዛል። አምባ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፤ ለጨቋኞች አልገዛም የሚል የእምቢተኝነት የሰላም የሕዝብ ጥሪውን ያስተላልፋል።
በሃሰት ትርክት ሰምጠው የድሉንም ደስታ ከኢትዮጵያውያን ዐዕምሮ ለመሰረዝ ለሊትና ቀን የሚባትሉ የከሰሩ የፖለቲካ ነጋዴዎችንና አድር ባይ ካድሬዎችን ያወግዛል ፡፡
የስልጣኔ ጮራ በኢትዮጵያ የፈነጥዕቁ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክና እቴጌ ጣይቱ በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ታቅፈውና ተደግፈው ያስመዘገቡት የአድዋ ድል፤ ዛሬ በአገራችን የሕዝብን ፍላጎትና እምነት የማይከተሉ መሪዎችን እንቅልፍ ቢነሳም፤ መላው ዓለም ክቡር ታሪካቸውን ሲዘክር ይኖራል።