በምስራቅ አማራ ውድመት እያደረሰ ያለውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር የመንገስት ግዴልሽነት ይብቃ

Image removed.

ምስራቅ አማራ ውድመት እያደረሰ ያለውን  የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር የመንገስት  ግዴልሽነት ይብቃ

 

በምስራቅ አማራ (በወሎና፣ ሰሜን ሸዋ ) ተከስቶ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ የሚገኘውን የአንበጣ መንጋ የአካባቢውም ሆነ የፌደራል መንግስት አይቶ እንዳላየ በቸልተኝነት እየተመለከተው ይገኛል። ከወራት በፊት ጀምሮ፣ የተለያዩ አለም አቀፍ የግብርና ምርምር ተቋማት የከፋ የአንበጣ መንጋ ወረራ በአካባቢው ሊከሰት እንደሚችል መተንበያቸው እና አስፈላጊውን ዝግጅት መጠቆማቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።  ከዚያም አልፎ አንበጣው ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ እስካሁን በእንጭጩ መቆጣጠር የሚቻልበት እድል ብዙ የነበረ ቢሆንም፣ የአካባቢውና የፌደራል መንግስት በሚያሳዪት ከፍተኛ ዳተኝነት የተነሳ፣ ደጋማው የምስራቅ አማራ ጭምር፣ በተለይም የወሎና የሰሜን ሸዋ አካባቢ፣ ከፍተኛ ውድመት እያስተናገደ ይገኛል። 

ገበሬው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ፣ ብዙ ወራት ደክሞ ያደረሰውን እህል ለምግብ፣ ለልብስ፣ ለልጆች ትምህርትና ለቀጣይ አመት ዘር ጭምር ሙሉ ተስፋ እያደረገው ሰብሉ በሰዓታትና በቀናት  ውስጥ በመውደሙ ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ ተስፋ መቁረጥና የአደጋ ተጋላጭነት እየደረሰበት እንደሚገኝ አረጋግጠናል። አመቱን ሙሉ ለፍቶ፣ ሌላ አመት የሚዘልቅበትን ሰብል ሙሉ በሙሉ ያጣው ገበሬ፣ በቀናት ውስጥ፣ የሚላስና የሚቀመስ የማይኖረው እንደሚሆን እሙን ነው። የዚህ አይነት የሰፊው ገበሬ ረሀብ፣ ከፍተኛ የሀገር ድህነት፣ ስደትና በሽታ፣ በተለይም ደግሞ የህጻናትና የእናቶች ሞትና ጉስቁልና የሚያስከትል መሆኑ ይታወቃል።

አድማሱን እያሰፋ የሚገኘው ይህ የአንበጣ መንጋ ያደረሰው ውድመት እንዳለ ሆኖ፣ በቀጣይም ወደሌሎች ያልተዳረሱ አካባውቢዎች የመዛመት እድሉ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ስለሚታወቅ፣ መንግስት የሚከተሉትን እርምጃዎች በአፋጣኝ እንዲወስድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

1.  መንግስት በአፋጣኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ፣ በቂ ሄሊኮፕተሮችና የሰው ሀይል ችግሩ ወደ ተፈጠረባቸው አሰማርቶ  የአንበጣውን መንጋ ይቆጣጠር፤

2.  አንበጣው ምርታቸውንና የከብቶቻቸውን መኖ አውድሞባቸው ተስፋ ቆርጠው ለሚገኙ ብዙ ሺህ የወሎና የሰሜን ሸዋ ገበሬዎች፣ መንግስት አስቸኳይ የዕለት ቀለብና ዘለቄታዊ ማቋቋሚያ እንዲያደርግና ችግሩ የሚያስከትለውን ማህበራዊ ቀውስ በአፋጣኝና በዘላቂነት እንዲያረጋጋ ጥሪ እናደርጋለን።

 

ከዚህ በተጓዳኝ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንበጣው መንጋ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ገበሬዎች ለማገዝ በሙሉ ሀይል እንዲረባረብና ማህበራዊ ቀውስ የመቀልበስ አስተዋጽዖ እንዲያደርግ በትህትና እንጠይቃለን።

 

አምባ - የአማራ ባለሞያዎች ማህበር
ዋሽንግተን ዲሲ

ቀን ፡ ጥቅምት 3 2013 ዓ.ም.

Lanaguage
Off