ይህ የአማራን “ክልል” የጤና ሁኔታ ለመዳሰስ የተካሄደ አነስተኛ ጥናት የ “ክልሉን” የጤና ሁኔታ በሙሉ ለማሳየት ፍጹም በቂ ነው ባይባልም፣ አሁን አገራችን እያካሄደች ካለችው ለውጥና የ “ክልሉ” መንግስትም የህዝቡን ችግሮችና ጥያቄዎች ለመመለስ ካሳየው ተነሳሽነት አንጻር ያሉትን ጉልህ ችግሮች በማሳየት የውይይት መድረክ ለመክፈትና ሁሉም የበኩሉን አስተዋጾ እንዲያደረግ ለመጠቆም መነሻ እንዲሆን የቀረበ ነው። በዚህ ዳሰሳ ውስጥ የተመለከቱት ጉድለቶች ለአማራ “ክልል” ህዝብ በልማት ወደኋላ መቅረት ምክንያቱ አጠቃላይ የስርአቱ አድሉዊነት እደሆነ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። “ክልሉን” የሚያስተዳድርው ብአዴንም(አሁን አዴፓ ተብሏል) ለአማራ ጥቅም ከመቆም ይልቅ ለትህነግ ተልኮ አስፈጻሚነት ቆሞ እንደቆየ በስፋት የተባለውን ማሳያ ነው።
ትህነግ (በተለምዶ ወያኔ) ጠባብና መንደርተኛ ጸረ ኢትዮጵያ፤ ጸረ አማራ አላማውን ይዞ ደደቢት ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ ህዝብ ላይ ያልሸረበው ገመድ፤ ያልቆፈረው ጉድጓድ፤ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። በደደቢት የድርጅት ፕሮግራሙ ላይ የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጇል፤ ጫካ እያለ የወልቃይት አማራዎችን በማንነታቸው ምክንያት ብቻ ሽዎችን ያለርህራሄ ገድሏል፤ አደህይቷል፤ አፈናቅሏል፤ በመሬት ውስጥ ማጎሪያው ለአመታት አሰቃይቷል። አሁንም ቁጥራቸው የማይታወቅ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በመሬት ውስጥ እስር ቤቶች በስቃይ ላይ እንዳሉ ይታመናል።
ትህነግ የአገር መግዛት ስልጣኑን እንደተቆጣጠረ የመጀመሪያው ተግባሩ አገሪቷን በዘርና በቋንቋ መተልተል ነበር። በዚህም ተግባሩ አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ እንዲፈጠር አድርጓል። በሰኔ 1983 ዓ.ም. ባደረገው ጉባኤ ላይ ይነስም ይብዛ ሁሉም ሌሎች “ብሄሮች/ብሄረሰቦች/ህዝቦች” በተቋቋመው የሽግግር መንግስት በምርጫም ባይሆን በስማቸው በተደራጁ ቡድኖች በኩል ውክልና ሲያገኙ የአማራ ህዝብ ግን ውክልና ሳያገኝ ቀርቷል። በዚህና ጸረ አማራው ትህነግ (ወያኔ) አዛዥ ናዛዥ በመሆኑ ምክንያት በርካታ አማራ የሚኖርባቸው አካባቢዎች ለሌሎች ቋንቋ ተናጋሪ “ክልሎች” ተሰጥተዋል። በዚህ ጊዜ ነው ወልቃይትና ጠገዴ ከሰሜን ጎንደር፤ ራያና ቆቦ ከወሎ ወደትግራይ የተከለሉትና ሌሎችም በርካታ አማራ የሚኖርባቻው አካባቢዎች ለሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች የተሰጡት። አማራም ከአያት ቅድመ አያቶቹ ጀምሮ በኖረባቸው ቀየዎች እንደጠላት ተቆጠረ፤ ተባረረ፤ በጅምላ ተገደለ። ልጆቹ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ ተከለከሉ። በአካባቢው ቋንቋ ተምረውም ከሌሎች ያላነሰ ቋንቋውን ተናግረውም “ክልላችሁ” አይደለም አያት ቅድመ አያቶቻቸው ከተወለዱበት ቦታ “አገራችሁ አይደለም” ተብለው የስራ እድል እንዳያገኙ ተከለከሉ። በዚህም ምክንያት ተሰደዱ፤ ለባርነት ተደረጉ፤ ተዋረዱ።
ሙሉውን ጥናት ከታች የተያያዘው ሰነድ ውስጥ ያገኙታል።