ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔር ከእስር ያስፈታቸዉን ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንኳን ደስ አላችሁ እያልን፤ በአሁኑ ሰዓትም ማህበራዊ ሚድያ ያላወቃቸው እጅግ በጣም ብዙ የሚሆኑ ሽማግሌዎ፣ ወጣቶች፣ የፓለቲካ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዋች፣ ጋዜጠኞችና የሀይማኖት አባቶች በፌደራል እና በክልል እስር ቤቶች እንደሚገኙ በቅርብ ከተፈቱት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምስክርነት ለመረዳት ችለናል።
አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች። መንግስት እስረኞችን በከፊል በመፍታቱ የተስፋ ጭላንጭል የታየ ቢመስልም መሠረታዊ የሆነው የሀገራችን የነፃነትና እኩልነት ችግር እንዳለ ነው። በታቀደና በተጠና መንገድ የጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን መልቀቅ እና በማግስቱም የዜጎችን የመሰብሰብ፣ የመሰለፍ፣ ሀሳባቸውን በነጻ የመግለጽ እና በማንኛውም መልክ መረጃ መለዋወጥን የሚከለክል፤ እንዲሁም ወታደሮች በዜጎች ላይ የፍርድ ቤት ትእዛዝ ሳይሰጣቸው በግብታዊና ድንገተኛ ሁኔታ እንዲፈትሹ፣ ምርመራ እንዲያደርጉ፣ እንዲያስሩ እና እርምጃ እንዲወስዱ ስልጣንን የሚሰጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ አገሪቱ ወደ ወታደራዊ ዕዝ እየገባች ስለመሆኑ አይነተኛ ማሳያ ነው። በዚህም ምክንያት አገራችን ኢትዮጵያ ወደ ትልቅ እስርቤትነት እንደተቀየረች ግልፅ ነው። ጉዳዩም አገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ ለሁላችንም እጅግ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታየውን የተስፋ ጭላንጭል ከጅምሩ ከድጡ ወደማጡ ይዞት እንደሚጓዝና አገራችን የማትወጣው የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንደሚከታት ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ እንዳይከስት ብልህ ከታሪክ ይማራል እንዲሉ ሆደ ሰፊ በመሆን ልክ እንደ ደቡብ አፍሪካ መሪ ኤፍ ደብልዩ ዲ ክለርክ የፓለታካውን ምህዳር ማስፋት አማራጭ የሌለው እርምጃ ነው። ከጫፍ እስከጫፍ የተነቃነቀው የህዝብ ተቃዉሞ የተለመደው አይነት ጥገናዊ ለውጥ የሚመልሰው ሳይሆን መሠረታዊ የስርዓትና ሥርነቀል አስተዳደራዊ ለውጥን የሚሻ ነው። በሰላማዊ መንገድ አስፈላጊውን ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣትም በቅድሚያ የማሻሻያ ለዉጥ ማድረግ ያስፈልጋል። ነገር ግን ለማንኛውም የማሻሻያ ለውጥ ሃሳብ ፍሬ እንዲኖረው ለውጥ ፈቃጅ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡ ስለሆነም መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚከተሉትን እንዲያደርግ አጥብቀን እናሳስባለን።
• በመገናኛ ብዙኃን የማይታወቁ ብዙ እሥረኞች ዛሬም በየወህኒ ቤቶች እንደሚገኙ ይታወቃል። የጋራ መግባባት ለማምጣት ሲባል ሁሉም የተቃዋሚ አባላት፣ የሰብአዊ መብት ታጋዮች ፣ ጋዜጠኞችና የዋልድባ ገዳም መነኮሳት፣ አንዳርጋቸው ጽጌና ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ ሌሎችም በማናቸውም ፖለቲካዊ አመለካከታቸው የተነሳ የታሰሩ ሁሉም ዜጎች እንዲፈቱ፤
• መጻፍ፣ መናገር፣ መደራጀት፣ ጥያቄ መጠየቅ፣ መልእክት መለዋወጥ፣ ቅሬታ ማሰማት፣ ሰልፍ እና ስብሰባ ማካሄድን ጨምሮ በመሠረታዊ መብቶች ላይ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስቸኳይ እንዲሻርና፤ የዜጎች መብት የሆነዉ ሰላማዊ ትግል እንዲቀጥል እንዲፈቀድ፤
• የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች በህዝቡ መካከል በነጻነት የመወያየት እና አጀንዳቸውን ለህዝብ የማስተዋወቅ መብት እንዲኖራቸውና ህዝቡም አማራጮች ሊኖሩት ያስፈልጋል፡፡ መንግስትም ሀገሪቱን ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠዉን አማራጭ የፓለቲካ ሀይሎችን የማሳደድ ባህል በአስቸኳይ አቁሞ ድጋፍና ጥበቃ እንዲያደርግላቸዉ፤
• የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች ምንጭ የሆኑት ተቋማት ማለትም የሀገር መከላከያ፤ የደህንነትና የፍርድ ሂደት የኃይል ስብጥርና አሰራር መስተካከል ይገባዋል። እነዚህ ተቋማት የአንባገነን አገልጋይነት ባህርያቸውን አስወግደው አገሪቱንና ህዝቧን በቁርጠኛነት ማገልገል በሚችሉበት መልኩ ማዋቀር ተጠያቂነትን ስለሚያስከትል መንግስትን የህዝብ አገልጋይ ማድረግና ለሰላማዊ ሽግግር የሚመች ፍትሃዊ ስርዓትን ማዋቀር እንዲቻል፤
• እንዲሁም ለብዙዎቹ የችግሮች መነሻ የሆነዉን የጎላ ችግር ያለበትንና ለሀገሪቱ የማይመጥነውን "ህገ መንግስት" ለኢትዮጵያ ህዝብ እኩል በሚጠቅምና የሀገር ህልውና፣ ሰላም አንድነትና ብልፅግና በሚያጎናጽፍ ህገመንግስት ለመቀየር ከህዝቡ በሚውጣጡ ታዋቂ ግለሰቦች፤ የሀገር ሽማግሌወች፤ምሁራን፣ ባለሙያወች፤ የታሪክና ህግ አዋቂዎች፣ አገርበቀል የፖለቲካ ሳይንቲስቶች እና ፖለቲከኞች እንዲቀርጹ በማድረግ ረቂቁንም ህዝብ እንዲወያይበት ለማድረግ ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት እንዲያሳይ፤
• ላለፉት ፳፯ ዓመታት ለተፈጠረው ከፍተኛ የህይወትና የንብረት ጥፋት ዋና ምክንያት የሆነው በዘር(በዘውግ) የተከፋፈለ አገዛዝ ያስከተለው አገራዊ ቀውስ ነው። ይህ ገና ከመነሻው የተዛባ አስተሳሰብ በበርካታ ዜጎች ላይ ታሪካቸውንና ማንነታቸውን ያላገናዘበ ዘውግን በግድ ከመጫን ጀምሮ በተወለዱባት ሀገር ውስጥ ልዩ ተጠቃሚዎችን እና ልዩ ተበዳዮችን በዘውግ ህጋዊነት እንዲፈጠር አድርጓል። ለምሳሌ በአማራው ሕዝብ ላይ ለዘመናት የደረሰው የማፈናቀል የግድያና የማንነት ድምሰሳ በደል፣ በአኙዋክ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ እንዲሁም በቅርቡ በ"ኦሮሞ ክልል" እና በ”ሶማሌ ክልል" መካከል የተፈጠረው ችግር የዚህ ብልሹ ስርዓት ውጤቶች ናቸው። ይህ በአስቸኳይ መቆም አለበት።
• የደርግን መውደቅ ተከትሎ በኃይል የተጫነው የዘር (ዘውግ) "ፌደራሊዝም" እና የዘውግ አስተዳደራዊ አከላለልም አገዛዙ በስልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት ሁሉ ለበርካቶች የማንነት ጥያቄን እንዲያነሱ አድርጓል። አገሪቱን የሚያስተዳድረው ዘረኛ መንግስት ከፋሽስት ጣልያን በቀር በታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው በደልና ግፍ በሀገሪቱና ህዝቧ ላይ ፈጽሟል። በጅምላ ዜጎችን ማሰር፤ ማፈናቀል እና ማሸማቀቅ፤ ከተሞችን የጦር ቀጣና እስኪመስሉ መካናይዝድ ጦር ሠራዊት በማሰለፍ፤ ዳር ድንበር ለመጠበቂያ በጦር ሜዳ ብቻ ሊያገለግሉ በሚገባ መሳሪያዎች ሰላማዊ ሰዎችን መግደልና፤ ሰላማዊ ዜጎችን ማሸበር፤ አገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግስት የተባለው የእለት ተእለት ተግባሩ ሆኗል። መንግስት አገሪቱን አገሬ የሚልና ፤ አስተዳድርሃለሁ ለሚለው ህዝብም አካል ነኝ የሚል ከሆነ የህዝብን ጥያቄ አዳምጦ መፍትሄ የማበጀት ግዴታ አለበት። ከመጀመሪያውም የተሳሳተው ጽንሰሃሳብ ላስከተለው መዘዝ መፍትሄው የዘር/የዘውግ አገዛዝን ማቆም ነዉ ብለን እናምናለን፥ የዘር አገዛዝ ከመምጣቱ በፊት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በእርስ በርስ ግጭት የታወቀ አልነበረምና። የፖለቲካ ሥርዓት አወቃቀሩም ዘውግ (ዘር) ተኮር ፌዴራሊዝም ከሚሆን ሁሉንም የኢትዮጵያ ዜጎች በእኩልነት እና ፍፁም ነፃነት በሚያስተናግድ ስርዓት ቢተካ አገራችን ከብዙ ችግር ትድናለች፡፡
የዘውግ/ዘር ፌደራሊዝም ካሉበት ብዙ ችግሮች መካከል የሚከተሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
1. የዘር ፌደራሊዝም መሠረቱና ኩነቱ ሁለት ማንነቶች ናቸው [የጎሳና የሀገራዊ]። እነዚህ ማንነቶች የሚጋጩና እየተራራቁ የሚሄዱ ናቸው፡፡ የዘር ፌደራሊዝም ስሜትን የሚገዙ ትንንሽ ጠንካራ ማንነቶችን የሚያጋንን፤ ሀገራዊ ራዕይን የሚያቀጭጭ፤ የዜጎችን የጋራ ብሄራዊ ማንነት የማይጨበጥ ህልም የሚያደርግባቸው ሥርዓት ስለሆነ፤ ቀና ፌደራል መንግስት ቢኖር እንኳ ብሄራዊ አንድነትን ለማምጣት፣ ለሀገርና "ሌሎች ዘሮች" መስዋዕትነትን ለመክፈል ፍላጎት የሌለው ትውልድን ይፈጥራል። እንዲሁም በጥሬ ሃብት ክፍፍልና በመሳሰሉት ጉዳዮች ለግጭት ተጋላጭ ያደርጋል።
2. በዘር (በዘውግ) ራስ ገዝነት የአንድ ዘር ብቻ ጉዳይ አስፈፃሚ አስተዳደሮችን የሚፈጥር "ሌሎች ዘሮች"ን ከአጥር ውጭ በማስወጣት፡ ደህንነታቸውንና ሃብታቸውን ለአደጋ ይጥላል፤ ለሀገር አስተዳደርም ሆነ ኢኮኖሚ መፈራረስም ይዳርጋል፡፡
3. የዘር ፌደራሊዝም በተመሳሳይ መልኩ ለግለሰቦች ሰብአዊ መብቶች መከበር ፀር ነው፡፡ ዘርና ጂኦግራፊ ባልገጠሙበት እንደ ኢትዮጵያ አይነት ሀገር: ግለሰቦች ብዙሃን ነን በሚሉ አስተዳደሮች "እንዳልተፈለገ አረም" ፣ "እንደመጤ" ፣ "በስህተት እንደተገኙ" በማስቆጠር ለማግለል፣ ለእንግልት፣ ለሞት፣ እና ለዘር ፍጅት ይዳርጋሉ።
4. ከተለያዩ ዘሮች (ዘውጎች) የተወለዱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ዘር (ዘውግ) መወሰን ስለማይቻል በግድ የሚለጠፍባቸው ዘር (ዘውግ) በተምታታበት ማንነት ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል።
ይህም ሲባል ግን ዘር (ዘውግ)፣ ቋንቋ እና ባህል እውቅና አይሰጠው ማለት አይደለም። የዘውግ (የዘር) ማንነት አስፈላጊ የግልና የወል መገለጫ ነውና የዘውግ (የዘር) ማንነት በማንኛውም ዘር (ዘውግ) ተኮር ባልሆነ አስተዳደር ሊከበርና ተገቢው ቦታ ሊሰጠውይገባል። በዘውጎች መካከል የአስተዳደር አጥር ባልሰራ መንገድ ሊገለፅና፣ ባህል ቋንቋውና ማህበራዊ እሴቶች እንዲያድጉና እንዲጠበቁ ይገባል፡፡ ይልቁንም ከላይ እነደተገለጸው ከህዝቡ በሚውጣጡ ታዋቂ ግለሰቦች፤ ያገር ሽማግሌዎች፤ ምሁራን፣ ባለሙያዎች፤ ታሪክና ህግ አዋቂዎች፣ በአገርበቀል ፖለቲካ ሳይንቲስቶች እና ፖለቲከኞች ጠቋሚነትና አርቃቂነት የተለያዩ የፓለቲካ አስተዳደር መዋቅሮች አዲስ ለሚመረጡ የህዝብ ተወካዮች ቀርቦ በህዝብ ሊወሰን ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ዋናው የህዝቡ ጥያቄ ለ፳፯ አመታት ሳያፈናፍን ስልጣን ላይ የቆየውን፣ በመንግስት ስም ሀገር ዝርፊያ ላይ የተጠመደውንና ሕዝብን የሚከፋፍለውን የህወሓት/ኢህአዴግን ስርዓት በቃህ የሚል ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ «ከኔም ወዲያ …..» የሚለውን አምባገነናዊ አስተሳሰብ እና እኔ አውቅላችኋለሁ ማለትን ትቶ ህዝቡ በመረጠው መተዳደር እንዲችል መንገዱን ክፍት ማድረግ ይጠበቅበታል። በቀጣይ ሁሉን አቀፍ የሆነና ከህዝቡ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዋች፣ ከማንኛውም የሚመለከተው አካል አና ሲቪክ ማህበራትንም ጭምር ያማከለ ውይይት በማድረግ የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ ፍትሃዊ፣ ነፃና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ በማድረግ ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲና መረጋጋት እንድትገባ ማድረግ ለተከሰተው ሀገራዊ ችግርና የሕዝብ ጥያቄ ብቸኛው አማራጭ ነው ሲል አምባ የአማራ ባለሙያዎች ማህበር ያሳስባል፡፡